መልስ የሚያሻው የእኛ የመምህራን ጥያቄ
ባለፉት 26 አመታት ተደጋጋሚ ስህተቶችን በመሥራት ከስህተቱ ሳይማር ዛሬም በሥልጣን ላይ የሚገኘው ገዢው ፓርቲ ዛሬም ከአንድ መንግሥት ነኝ ባይ የማይጠበቅ ተግባር በመፈፀም ላይ ይገኛል። መምህራን ተደራጅተን በሠላማዊ መንገድ ጥያቄያችንን እንዳናቀርብ አንጋፋውን የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ከእውነተኞቹ ተወካዮቻችን ከእነዶክተር ታዬ ወልደሰማያት እና አሠፋ ማሩ ተቀብሎ በገንዘብ ህሊናቸውን ለሸጡ የመምህሩ ጉዳት እና የትውልዱ ምክነት ለማይሰማቸው የተወሰኑ የኢህአዴግ አባላት በመስጠት መምህሩን ያለተወካይ ማስቀረቱ እሙን ነው። ከሰሞኑም ከደመወዝ ጭማሪው በመንግሥት አጠራር ማስተካከያ ጋር በተያያዘ እኛ መምህራን ያለንን ጥያቄ በተወካዮቻችን አማካኝነት እንዳናቀርብ ኢህአዴግ ጠፍጥፎ የሰራው ተለጣፊው የመምህራን ማህበር እንቅፋት ሆኖ ይገኛል። በዚህም የተነሣ መምህራን መብታችንን ለማስከበር በሕቡዕ መንቀሳቀሱ የተሻለ መሆኑን ተረድተን የራሳችንን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የምንገኝ ሲሆን በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል ከሰሞኑ የተጀመሩት የሥራ ማቆም አድማም የዚህ ውጤት ነው። በመሆኑም የስራ ማቆም አድማው በሰፊው ተቀጣጥሎ ንጹሃን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ከመራቃቸው በፊት መንግሥት ነኝ ባዩ ኢህአዴግ የሚከተሉትን ጥያቄዎች በአፋጣኝ ሊመልስ ይገባል እነርሱም፦
1, በአሁኑ ሰአት በሃገራችን ለተመሳሳይ የትምህርት ደረጃዎች የሚከፈለው ደመወዝ ልዩነት እጅግ የተጋነነ ልዩነት የሚታይበት ነው። ለዚህም እንደማሳያ 20 አመት የሰራ መምህር ደመወዝ ከ6000 ብር የማያልፍ ሲሆን ጀማሪ የመጀመሪያ ዲግሪ ያለው አንድ የወረዳ ተራ ካድሬ መነሻ ደመወዝ ግን ከ6000 ብር በላይ ነው። እንደዚህ አይነት የተጋነነ ልዩነት ባለበት ሁኔታ የመምህራን መብትረ ተከብሯል ማለት ስለማይቻል መንግሥት በአፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስድ፡፡
2, በቅርቡ በአዲስ አበባ ለሚገኙ መምህራን ተከፋፈለ የተባለው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ እጅግ ሲበዛ ኢፍትሃዊ የነበረና መንግስትን ይቃወማሉ ተብለው የሚታሰቡ መምህራን እጣው ውስጥ እንዳይሳተፉ በክፍለ ከተማ አመራሮች የተደረጉ በመሆኑ መንግሥት በሚዲያ ይቅርታ በመጠየቅ ስማቸው ከእጣ ውጭ የሆኑ መምህራን የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርበታል።
3, ተለጣፊው የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር በአስቸኳይ ፈርሶ ሁሉንም መምህር ባሳተፈ መልኩ በገለልተኝነት የሚሰራ የመምህራን ማህበር በአስቸኳይ ይቋቋም ዘንድ መንግሥት ቅድመ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይኖርበታል።
4, ከሰሞኑ ከመምህራን የሥራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ ለእስር የተዳረጉ መምህራን ባልደረቦቻችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በነፃ ሊለቀቁ ይገባል እያልን ያቀረብናቸው ጥያቄዎች በአግባቡ የማይመለሱ ከሆነ በሰሜኑ የሃገራችን ክፍል በተለይም በአማራ ክልል የተጀመረው የሥራ ማቆም አድማ
በሌሎችም አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል እየገለፅን የተቃዋሚ ፓርቲዎች ደግሞ የእኛን የመምህራን ጥያቄ በማንሻፈፍ ለፖለቲካ ፍጆታነት ለመጠቀም የምታደርጉትን ጥረት እንድታቆሙ እየገለፅን የመምህሩን እንቅስቃሴ እና ትግል የመምራት አንድም ፓርቲ ፍላጎቱ እና አቅሙ እንደሌለው ለማሳሳብ እንወዳለን።
የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሰማ ጊዜያዊ ኮሚቴ የካቲት/30/2009 አመት ምህረተ አዲስ አበባ ኢትዮጵያ