ድኅረ ምርጫ 97 እና ኢሕአዴግ

Standard

           ድኅረ ምርጫ 97፣ ኢሕአዴግ ኢኮኖሚውን ጠቅልሎ ለመያዝ (monopolize ለማድረግ) የተረባረበበት ጊዜ ነው። ከዚያ በፊት እንደ ትእምት ዓይነቶቹ ቢኖሩም፣ በይፋ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች እንዲከብሩ፣ ተቃዋሚዎች እንዲከስሩ የተደረገው ከ97 በኋላ ነው። በ1997ቱ ምርጫ ወቅት ተቃዋሚዎችን የረዱ ነጋዴዎች ቀስ በቀስ ተመቱ። መንግሥት ራሱን “ልማታዊ” ነኝ ብሎ ከሾመ በኋላ፥ ለስርዓቱ አካሔድ የተመቹትን ነጋዴዎች “ልማታዊ” ሲላቸው፣ ያልተመቹትን ደግሞ “ኪራይ ሰብሳቢ” ብሎ መደባቸው። ከላይኛው ከበርቴዎች ጀምሮ እስከታችኛው ጥቃቅንና አነስተኛ አደረጃጀት ድረስ የስርዓቱ መዋቅር ማጠናከሪያ ሆኑ። የተለያዩ ሊጎች ሲመሠረቱ፣ የኢሕአዴግ ደጋፊ ነጋዴዎች ሊግም አብሮ ተመሥርቷል። በዚህ አጋጣሚ ሙስና እንደጉድ ተስፋፋ።
ይህን ሁነት ተቃዋሚዎች የስርዓቱን የሞራል ዝቅጠት ማሳያ አደረጉት። ኢሕአዴግ የመንግሥት ሚዲያውን የፕሮፓጋንዳ ማሺን ቢያደርገውም፣ ተደማጭነት እና ታማኝነት ሊያገኝለት አልቻለም ነበር። ከ1997 በኋላ የተቃዋሚውን ሚዲያ ማዳከምና ማጠልሸት ላይ እንጂ በትርክት እና ተደማጭነት በልጦ መገኘት ላይ አልሠራም ነበር። የ2008ቱ ሕዝባዊ አመፅም በፖለቲካ ትርክት የመበለጥ እንደሆነ ኢሕአዴግ ገብቶታል። ስለዚህ፣ በድኅረ 2008ቱ አመፅ ጊዜ፣ የሚዲያ እና የትርክት ጠቅላይነት እንቅስቃሴውን መጀመሩ የማይቀር እንደሆነ አመላካች ሁኔታዎች አሉ፣
1ኛ፣ የማኅበራዊ ሚዲያው መታገድ (በፕሮክሲ ካልሆነ አይታይም፤ በፕሮክሲ ለሚመለከቱ ሰዎች ተፎካካሪ ትርክት ለመስጠት የተዘጋጁ ሚዲያዎች ፌስቡክ ላይ ተከታያቸውን አብዝተዋል። ኤፍቢሲ ጥሩ ምሳሌ ነው።)
2ኛ፣ ዳያስፖራ ተቀማጭ ሚዲያዎች መታገድ (በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታገዱት ኢሳት እና ኦኤምኤን አሁን ደግሞ ክስ ተመሥርቶባቸዋል። የአዋጁ ጊዜ ሲያልቅ በፍርድ ቤት እንዲታገዱ ይደረጋል።)

3ኛ፣ ለዘብተኛ የሚመስሉ ነገር ግን ለገዢው ፓርቲ የሚወግኑ ሚዲያዎች መብዛት። (ፋና የቲቪ ፈቃድ አግኝቷል፤ ዋልታ ቲቪ የሙከራ ሥርጭት ጀምሯል፤ የማንነቱ ያልተለየው እና ፋናን መሳዩ ኢኤንኤን ቲቪ ሥራ ጀምሯል።)

4ኛ፣ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሚዲያዎች ተቀባይነታቸውን ለማሻሻል በመጠኑ ተቺ ይመስላሉ። (ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ ዘመን የሽፋን ገፅ ዜናዎች፣ ‘የኮንዶሚኒየም አሠራር ካልታረመ ለተመዘገገቡት ማዳረስ እንኳን 55 ዓመት ሊፈጅ እንደሚችል’ እና የመሳሰሉትን መናገሩ የዚህ ጥረት አንድ አካል ነው።
ድኅረ 97 ለተቃዋሚውም ለገዢውም መማሪያ ነው። ከ97 በኋላ በፓርቲ ፖለቲካ ተስፋ የቆረጠው ሕዝብ፣ ማንም ሳያደራጀው ተቃውሞውን  ገልጿል። ሕዝባዊ ተቃውሞው በኃይል ከታፈነ በኋላ ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሚወለድ መገመት ከባድ ነው። ሚዲያውን እና የፖለቲካ ትርክቱን በበላይነት መቆጣጠር በመጪው ዐሥር ዓመታት የሚሆነውን በጉልህ ይወስናል። ይህ ለኢሕአዴግ ከወዲሁ የገባው ይመስላል።

©Befekadu Zehailu

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.