ALERT ON REMITTANCE TRANSFERRING SYSTEM! የአገራችሁ የወደፊት እጣ ፋንታ ለሚያሳስባችሁ እና የህዝባችን የመከራ ጊዜ እንዲያጥር ለምትፈልጉ ኢትዮጵያዊያን

Standard

ከየአቅጣጫው የሚመጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የሚመራዉ አገዛዝ ግዙፍ በሆኑ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የደህንነት/የጸጥታ ቀውሶች ውስጥ የተዘፈቀበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ይፋ እየሆነ እንደመጣው በሁሉም ኢኮኖሚያዊ መገለጫዎች እና መለኪያዎች ስርዓቱ ከባድ ችግር ውስጥ ገብቷል። ይህን ቀዉስ አገዛዙን ከፍተኛ ስጋት ላይ እንደጣለዉ፣ በቅርቡ የብሄራዊ ጸጥታ ም/ቤት ተብሎ ከሚታወቅ አካል ሾልኮ የወጣ ሰነድ ያረጋግጣል።

ሰነዱ፥ በሰብአዊ መብቶች መረገጥ ሳቢያ የውጭ እርዳታ እየቀነሰ መምጣቱን፣ ሀገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው አለመረጋጋት የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ መቀነሱን፣ ባለሃብቶች እና ኢንቨስተሮች ገንዘባቸዉን ወደዉጭ ማሸሽ እንደጀመሩ እና በሌሎችም ምክንያቶች አጠቃላይ የኢኮኖሚ ድቀት መፈጠሩን አምኖ ያትታል። በሌላ በኩል፣ የብሄራዊ ባንክ ገዢ፣ ለህወሓት ፓርላማ ባቀረበዉ ሪፖርት፣ ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሬ እጥረት መኖሩን አመልክቶ ይህ እጥረት ባጭር ጊዜ ዉስጥ መፍትሄ ካልተገኘለት፣ የኢኮኖሚ ቀዉሱን እንደሚያባብሰዉ አስረድቷል።

በአሁኑ ወቅት የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ እጅግ በመባባሱ የተነሳ ቴሌኮሙዩኒኬሽንን የመሰሉ የአገዛዙ የአፈና ተቋማት ሳይቀሩ ብድራቸውን መክፈል ያልቻሉበት እና ስራቸውን በአግባቡ ለመወጣት አዳጋች የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። በብሄራዊ ባንክ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከ 3 ቢሊዮን ዶላር ወደ 700 ሚሊዮን ዶላር በመውረዱ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች ከውጭ እቃ ለማስገባት የክፍያ ስምምነት (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) ለመክፈት ከዓመት በላይ እንደሚጠብቁ እና ከዛም በኋላ የጠየቁትን ያክል ገንዘብ ማግኘት እንደማይችሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ይሁንና ባሁኑ ወቅት፣ ሌሎች የዉጭ ምንዛሬ ምንጮች እየደረቁ ቢሆንም፣ አገዛዙ ተስፋ የጣለብት በውጭው አለም ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገር ውስጥ የሚገባው ገንዘብ ወይንም ሬሚታንስ (Remittance) ነዉ። የዚህ ሬሚታንስ መጠን ባሁኑ ጊዜ በአመት ከ 4 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን አገዛዙ ይፋ አድርጓል።

ስለዉጭ ምንዛሬ ሲነገር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ሊያስብ የሚገባቸዉ መሰረታዊ እዉነቶች፥-

የሀገሪቱን ሀብት እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሰፊዉ ተቆጣጥረዉ፣ የዉጭ ንግዱንም ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚቻል ደረጃ ይዘዉ ያሉት <ኤፈርት፣ የትግራይ ልማት ድርጅትና የትግራይ ተራድዖ ማህበር> ተብለዉ የሚታወቁት፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የህወሓት ሃብት የሆኑት የኢኮኖሚ ድርጅቶች መሆኑን፣ የሀገሪቱ የዉጭ ምንዛሬ መጨመር ወይም መቀነስ ከሁሉ በፊት የሚጠቅመዉ ወይም የሚጎዳዉ እነዚህን ድርጅቶች እና በስራቸዉ የሚገኙ በርካታ ኩባንያዎች መሆኑን፣ የአገዛዙ የኢኮኖሚ ድቀት፣ ህዝብን ለመጨቆን፣ ለማፈን እና ለመግደል የሚጠቀምባቸዉን የደህንነት፣ የፖሊስ እና የልዩ ጦር ቁሳዊ፣ ቴክኖሎጂካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚነሳ መሆኑን እና፣ የአገዛዝዙን የፖለቲካ እድሜ ለማሳጠር፣ የኢኮኖሚ አከርካሪዉን መምታት የግድ መሆኑን እና የዉጭ ምንዛሬ እጥረትም የሚጫወተዉ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ነዉ።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚገነዘበው፣ በዚህ ወቅት ህዝባችን ነጻነቱን ለማግኘት እና የሀገሩ ባለቤት ለመሆን ከፍተኛ መስዋእትነት እየከፈለ ይገኛል። ከሁለት አመት በላይ የዘለቀው ህዝባዊ እምቢተኝነት ህዝቡን ውድ ዋጋ ቢያስከፍለውም የህወሓትን መንግስት ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ አስገብቶታል። ከላይ የተዘረዘሩት አገዛዙ የገባባቸው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የህዝቡ የትግል ፍሬዎች ናቸው። ነገር ግን፣ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ያለው የህዝባችን ትግል ለድል እንዲበቃ የሁሉላችንንም ርብርብ ይጠይቃል። በተለይም በውጭ ሀገራት የሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን የአገዛዙን ኢኮኖሚያዊ እና ብሎም ፖለቲካዊ አቅም የማንኮታኮት ከፍተኛ ሀይል አላቸው። ኢትዮጵያዊያኑ ወደ ሀገርቤት የሚልኩት ገንዘብ ወይም ሬሚታንስ አገዛዙ በአሁኑ ወቅት በዋነኛነት ተንጠልጥሎ የሚገኝበት ከፍተኛው የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ነው። በዚህ የውጭ ምንዛሬ ምንጭ ላይ በተለያዩ መንገዶች የሚደረግ እቀባ የስረአቱን የኢኮኖሚ ቀውስ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያባብስ እና የማፈን አቅሙን የሚያዳክም በኢትዮጵያዊያኑ እጅ ውስጥ ያለ ትልቅ አቅም ነው። በመሆኑም፣ የስርአቱ የኢኮኖሚ ቀውስ ተባብሶ የመግዛት አቅሙ እንዲዳከም እና ብሎም እንዲንኮታኮት እንዲሁም የህዝቡ መስዋእትነት ለድል እንዲበቃ እና የመከራው ጊዜ እንዲያጥር ውጭ ያሉት ኢትዮጵያዊያን ትልቅ ሀላፊነት አለባቸው።

ስለሆነም፣ የህዝባችን የመከራ ጊዜ እንዲያጥር የሚመኝ ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚከተሉትን ጥሪዎች ተግባራዊ ያድርግ!

እንደ ዌስተርን ዩኒዮን እና መኒ ግራም በመሳሰሉ መደበኛ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች እና ባንኮች/Formal Financial Transferring Channels/ አማካኝነት ዶላር፣ ዩሮ፣ ወይም ሌላ የውጭ ገንዘብ እንዳይላክ ማድረግ። በምትኩም፥ በሚከተሉት ኢ-መደበኛ የመላኪያ መንገዶችን መጠቀም የሚላከው ገንዘብ ከአገዛዙ አካውንት ውስጥ የመግባት እድሉ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ህብረተሰቡ በሚኖርበት አካባቢ እያፈላለገ መጠቀሙ ተመራጭ ነው።

ሀ) በየአካባቢው ገንዘብ በማስተላለፍ ስራ ላይ በተሰማሩ ቡድኖች ወይም ግለሰቦች በኩል መላላክ። ግን ደግሞ ሰዎቹ ከወያኔ ጋር ንክኪነት እንደሌላቸው ማረጋገጥ። ይህ ዘዴ በስፋት ስራ ላይ ያለ ውጤታማ የቅብብሎሽ ዘዴ ነውው።

ለ) አገር ቤት ያላቸውን ገንዘብ በተለያየ ምክንያት ወደ ውጭ ምንዛሬ ቀይረው በውጭ አገራት ማስቀመጥ በሚፈልጉ ሰዎች በኩል መላላክ። የዚህ አይነት ሰዎች በውጭ አገራት ዘመዶች ያሏቸው ሲሆን የገንዘብ ቅያሬውን የሚያከናውኑት በዘመዶቻቸው አማካኝነት ነው።

ሐ) የሚላከውን ገንዘብ ለተጓዦች መስጠት እና ኢትዮጵያ ውስጥ በጥቁር ገበያ መቀየር (የሚቻል ከሆነ ከወያኔ ጋር ንክኪነት ያላቸውን መንዛሪዎች መለዬት)።

መ) እንደ ላፕቶፕ፣ ሴልፎን የመሳሰሉ እቃዎችን ገዝቶ መላክ እና እቃዎቹ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሸጡ ማድረግ። ሁኔታዎች ሳይመቻቹ ቀርተው የግድ ዌስተርን ዩኒዮንን በመሳሰሉ የገንዘብ አስተላላፊ ድርጅቶች ገንዘብ መላክ ካስፈለገ፣ የቤተሰቦቻችሁን የኢኮኖሚ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት የምትልኩትን ገንዘብ መጠን /አማውንት/ ወይም ድግግሞሽ /ፍሪኩየንሲ/ በጣም እንዲቀንስ ማድረግ። ቢቻል በሀገር ቤት ያሉት ቤተሰቦቻችሁ በቂ ገቢ ያላቸው እና ከውጭ የሚላከው ገንዘብ ቢቆም የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ጫና ዝቅተኛ ከሆነ፣ የህዝቡን የሞት-ሽረት ትግል ለማገዝ ሲባል ገንዘብ መላካችሁን ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ማድረግ።

ከስርዓቱ ሾልኮ የወጣው የወያኔ ደህንነት ሰነድ እንዳመለከተው እና የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እንደሚያሳየው፣ ከሁለት አመት በላይ በዘለቀው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ሳቢያ የገንዘብ ሽሽት ተባብሶ ቀጥሏል። ሀገርቤት ያሉ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን ማሸሽ በጀመሩበት በዚህ ፈታኝ ወቅት፥ ለግንባታና ለንግድ በሚል ጠንካራ ገንዘብ /Hard Currency/ ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በድፍረት መናገር ይቻላል። ለንግድ እና ግንባታ የሚሆን የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገርቤት የምትልኩ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን፥ በድካም ያፈራችሁት ንብረታችሁ የተጋረጠበትን አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ንግዳቸሁን ወይም ግንባታቸሁን የኢትዮጵያ ሁኔታ እስኪለይለት ድረስ፥ እንድታቆሙ ለነጻነት በሚፈሰው የወገን ደም ስም አደራ ይሁንባችሁ!!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.