ህወሃት ያወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳይሰራ ማድረግ ቀዳሚ ተግባራችን ነው።

Standard

ከአርበኞች ግንቦት 7

ህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መላው ህዝባችን እየጠየቀ ያለውን የእኩልነትና የነጻነት ጥያቄ በወታደራዊ ሃይል ለመጨፍለቅና ላለፉት 27 አመታት የኖርንበት አይነት የግፍና የመከራ ዘመን ለማስቀጠል ወስኖ እንቅስቃሴ ለማድረግ መዘጋጀቱን የካቲት 8 ቀን 2010 ይፋ ባደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አረጋግጦአል።

በመላው አገራችን የተቀሰቀሰውን ይህንን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመጨፍለቅ ያስችለኛል ብሎ ህወሃት ያወጀው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበትን ወቅት ብንመለከት፤ የኢህአደግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በቅርቡ አድርጎት በነበረው አስቸኳይ ስብሰባ አገሪቱ ለገባቺበት የፖለቲካ ቀውስ ሙሉ ሃላፊነት ወስዶ መፍትሄ ፍለጋ ከሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር እንደሚነጋገርና የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በቁርጠኝነት እንደሚሠራ “ውሳኔ አስተላልፌያለሁ” ባለ ጥቂት ወራት ውስጥ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ላለፉት 6 አመታት የአገሪቱን ጠቅላይ ሚንስትርነትና የኢህአደግ ሊቀመንበርነትን ሥልጣን ይዞ የቆየው ሃይለማሪያም ደሣለኝ ለዚህ ውሳኔ ተገዥ በመሆን “ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር” ለማድረግ ይቻል ዘንድ “ሥልጣኔን በገዛ ፈቃዴ ለቅቄያለሁ” ብሎ ባስታወቀ ዕለት ማግሥት መሆኑ በሰፊው እያነጋገረ ነው ።

ህወሃት/ኢህአደግ በህይወት ዘመኑ ሁሉ ለቃሉ እንደማይታመን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ የሚያውቅ ቢሆንም የሃይለማሪያም ደሣለኝ የሥልጣን መልቀቂያ ጥያቄውን ይፋ ከማድረጉ ጥቂት ቀናት በፊት ጀምሮ አንድም ቀን እስከነመኖራቸው አገዛዙ ምንም አይነት እውቅና ሰጥቶ የማያውቅ በርካታ የፖለቲካና የሂሊና እስረኞችን መፍታት በመጀመሩ፡ ህወሃቶችና የሚመሩት መንግሥት ወደ ሂሊናቸው ተመልሰው ህዝባችን ለአመታት ሲታገልለትና ውድ ህይወቱን ሲገብርለት የኖረውን የዲሞክራሲ ጥያቄ ዕልባት እንዲያገኝ የራሳቸውን አስተዋጾ ለማድረግ የተዘጋጁ መስሎት አብዛኛው ህዝብ በትልቅ ተስፋና ጉጉት ሁኔታውን ሲከታተል ሰንብቶአል።

እስከ አገባደድነው ሳምንት አጋማሽ በአብዛኛው የኦሮሚያ፤ የአማራና አንዳንድ የደቡብ ከተሞች ህዝብ አደባባይ በመውጣትና ቤት ውስጥ በመቀመጥ አድማ ሲጠይቅ የነበረውም ይህ የተጀመረው እስረኞችን የመፍታት በጎ ጅምር ተፋጥኖ እስር ቤት የቀሩት ፖለቲካ እስረኞች በሙሉ እንዲለቀቁና ሁሉንም ያቀፈ ብሄራዊ ውይይት እንዲጀመርና አገራችን ከገባቺበት የፖለቲካ አጣቢቅኝ እንድትወጣ መፍትሄ እንዲፈለግ የሚያሳስብ ነበር።

ከፍጥረቱ ጀምሮ ለኢትዮጵያ አገራችንና ለህዝቧ ደንታ ኖሮት የማያውቀው ወያኔ ግን ህዝብ ተስፋ ያደረገውን ይህንን እድል ለማጨለምና የታገለለትን ዓላማ ለመቀልበስ ያስችለኛል ብሎ ያመነበትንና ከአመት በፊት ሞክሮ ያልተሳካለትን ወታደራዊ አገዛዝ አገራችን ላይ መልሶ ለማስፈን ህዝባችንን እያስቆጣ ያለ ይህንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደገና አውጆአል።

የንቅናቄያችን ሊቀመንበር ፕሮፈሰር ብርሃኑ ነጋ ይህንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስመልከተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ባስተላለፉት መልዕክት እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ህወሃት ላለፉት 27 አመታት በአገራችንና በህዝቧ ላይ ያመጣውን መዓትና የወረደውን ግፍ ለሀገር ሠላም ሲባል በብሄራዊ እርቅ ስሜትና እነርሱንም ባሳተፈ የድርድር ሄደት እንዲፈታ በሠላማዊ ህዝባዊ ትግል እየጠየቀ ባለበት ወቅት፣ ይህ አዋጅ መታወጁ ህወሓት/ኢህአዴግ ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል የሚሄድበት ርቀት ምን ያህል የእብደት መንገድ እንደሆነ የሚያሳይ” ብቻ ሳይሆን፣ በህወሃት ውስጥ ያሉ የአገዛዙ ቁንጮዎች እንወክለዋለን ሲሉ የኖሩትን የትግራይ ህዝብ ጨምሮ ከተጠናወታቸው የግል ጥቅም አስበልጠው የሚጨነቁለት ህዝብ ወይም አገር ፍቅር ስሜት የሚባል ነገር የሌላቸው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው።

ይህንን ሃቅ ያልተረዱ አንዳንድ ወገኖች እንደሚከራከሩት ህወሃት ውስጥ ትንሽም ቢሆን የህዝብና የአገር ፍቅር ስሜት ያላቸው የአመራር አባላት ቢኖሩ ኖሮ፣ ከሁለት አሥርተ አመታት በላይ ለዘለቀ ጊዜ ልዩ ልዩ የጠላትነት ታፔላ እየተለጠፈለት በጭካኔ ሲጨፈጨፍ ፤ ሲታሠር ፤ ሲገረፍ ፤ ከትውልድ መንደሩና ቄዬው ሲፈናቀልና ሲሰደድ የኖረው ህዝብ ለሠላም ሲል የተፈጸመበትን መከራና ስቃይ ፋይሎችን ሁሉ በብሄራዊ እርቅ ዘግተን እናንተንም ጭምር ያካተተ የሽግግር ምዕራፍ ይከፈት ብሎ ሲጠይቅ “ምን ታመጣለህ?” በሚል እብሪትና ጀብደኝነት ከራሱ ከህዝብ አብራክ የወጣውን የመከላኪያ ሠራዊት ህዝብ ላይ ለማዝመትና አገራችንን ወደ የርስ በርስ ብጥብጥ ለመክተት እንዲህ አይነት አፋኝ አዋጅ ባላወጀ ነበር።

ታጋሽ፣ ጨዋና አስተዋይ ይሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ እስከዛሬ ሲፈጸምበት የኖረውን መከራና ስቃይ ሁሉ ለሠላም ሲል ይቅር ብሎ ለህወሃት የይቅርታ እጁን የዘረጋው፣ ድርጅቱ ሥልጣን ከተቆጣጠረበት ጊዜ ጀምሮ በመብቱ፣ በብሄራዊ ጥቅሙና በሉአላዊነቱ ላይ ሲፈጽማቸው የኖረውን ግፍና ወንጀሎች ሁሉ ሳያሳምሙት ቀርተው አልነበረም። ወይንም ደግሞ ህወሃቶች እንደሚያስቡት የሚተማመኑበት ወታደር ብዛትና መሣሪያ ጋጋታ የጀግንነት ወኔውን ሰልቦት በባርነት እየተረገጠ መገዛትን ፈቅዶ አይደለም። የአጋዚ ጦር በጠራራ ጸሃይ የሚፈጽምበትን ጭፍጨፋ እየተመለከተ ግንባሩን ሳያጥፍ ላለፉት ሶስት አመታት ባዶ እጁን “ነጻነቴን መልስልኝ!” እያለ ከአገዛዙ ጋር ፊት ለፊት እየተጋፈጠ ያለው ለዚህ ምስክር ነው።

አርበኞች ግንቦት 7 ደጋግሞ ለመግለጽ እንደሞከረው ህወሃት እየገጠመው ከመጣው አገር አቀፍ ህዝባዊ ተቃውሞ በተጨማሪ በራሱ በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረው የጥቅምና የሥልጣን ሽኩቻ አንድነቱ የተናጋ ድርጅት ከመሆን አልፎ በገዛ አገራቸውና ወገናቸው ኪሳራ እስከ ዛሬ መሣሪያ ሆኖ ሲያገልግሉት የኖሩት የኢህአደግ አባል ድርጅቶች (በተለይም ኦህዴድና ብአዴን) ከአሁን ቦኋላ “የበላይነትህን አንቀበልም” ብለው አጣብቅኝ ውስጥ የከተቱት ድርጅት በመሆኑ፣ እንኳን ይህንን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመላው አገሪቱ ላይ ሊያስፈጽም ቀርቶ እንደ ድርጅትም ጸንቶ ለመቆየት የሚያስችለው አቅም እንደለለው ያምናል።

ይህንን አቅሙን የተረዱት ምዕራባዊያን ወዳጆቹ ሰሞኑን ባወጡት ጠንከር ያለ መግለጫ በአጉል ትዕቢትና ጀብደኝነት ተጠምዶ እራሱንና አገሩን ወደ ከፋ አደጋ ከመውሰድ እንዲታቀብና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአስቸኳይ አንስቶ ከሁሉም ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመደራደር አገራዊ መፍትሄ እንዲፈልግ አሳስበውታል። የህወሃት መሪዎች ምዕራባዊያን ወደጆቻቸውና የኢትዮጵያ ህዝብ እያቀረቡላቸው ያለውን ጥሪ ተቀብለው የህዝባችንን የለውጥ እንቅስቃሴ ከግብ ለማድረስ የሚያስችል እርምጃ ቢወስዱ እራሳቸውንና ድርጅታቸውን ከህግና ከታሪክ ተጠያቂነት ያድናሉ ፤ የለውጡ አካልም በመሆን ህልውናቸውንና ጥቅማቸውን ለማስከበር እድል ያገኛሉ። ይህ ዕድል እንዳያመልጣቸው ለህዝብ እንጨነቃለን የሚሉ አባላትና ደጋፊዎቻቸው በሙሉ አቅማቸው የሚችለውን ሁሉ ተጽዕኖ ሊያደርጉ ይገባል።

አርበኞች ግንቦት 7 ህወሃት ህዝባችንን ለማፈንና የባርነት አገዛዙን መልሶ ለማስፈን ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደ ከዚህ በፊቱ ፍጹም ሊሠራ የማይችል መሆኑን ለማሣየት ለመብቱና ለነጻነቱ እየተፋለመ ካለው ህዝባችን ጎን ቆሞ በሁሉም የትግል መስክ ተግቶ ይሠራል። በዚህም የተነሳ የኢህአደግ አባል ድርጅቶች ውስጥ እየታዩ ያሉ አንዳንድ የለውጥ ሃይሎች የሚያደርጉትን ጥረት ተስፋ አድርገው የሚጠባበቁ ካሉ፣ ይህ አዋጅ እነርሱንም ጭምር ጭዳ ለማድረግና በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ወታደራዊ አገዛዝ ለማስፈን የታለመ መሆኑን ተገንዝበው አዋጁ እንዳይሰራ ለማድረግ ከህዝባችን ጎን እንዲሠልፉ ወገናዊ ጥሪውን በየደረጃው ላሉ ለነዚህ የኢህ አደግ አባላትና ደጋፊዎች ያቀርባል ። ኦህዴድንና ብአዴንን በመወከል የአገሪቱ ፓርላማ አባላት ሆነው በማገልገል ላይ ያሉ የህዝብ ተወካዮች ነን የሚሉ ወገኖችም የህዝብን መብትና ስብዕና የሚጋፋ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በፓርላማው እንዳይጸድቅ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ጥረት ማድረግ እንደሚጠበቅባቸውም ያሳስባል። ይህንን ታሪካዊ ሃላፊ ነታቸውን መወጣት ተስኖአቸው አዋጁ እንዲጸድቅ ካደረጉ፣ በአዋጁ ምክንያት በአገራችንና በህዝባችን ላይ ለሚደርሰው በደል ከህወሃት እኩል ተጠያቂ እንደሚሆኑ እንዲገነዘቡም ያስጠነቅቃል።

ከህዝብ አብራክ የወጣው የአገራችን መከላኪያ ሠራዊት ፤ የፖሊስና የደህንነት ተቋም አባላትም በሙሉ ህወሃት የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ሲል ህዝባችንን እርስ በርስ ለማጋጨትና አገራችንን ወደ ትርምስ ለመውሰድ ያወጣውን ይህንን አፋኝ አዋጅ ፈጽሞ ሥራ ላይ እንዳይውል እንዲከላከሉና የሚሠጣቸውን ተእዛዝ እንዳይቀበሉ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 ወገናዊ ጥሪውን ያቀርብላቸዋል።

የትግራይ ህዝብን ጨምሮ መላው የአገራችን ህዝብ መውደቂያው የተቃረበው የህወሃት አገዛዝ ከፊት ለፊታችን የደቀነውን አደጋ በጋራ ለመመከትና ሁላችንም እኩል ተጠቃሚ የምንሆንባት አገር ባለቤት ለመሆን የሚደረገውን ትግል እስከመጨረሻው የድል ቀን ድረስ በቁርጠኝነት እንዲገፉ ንቅናቄያችን ወገናዊ ጥሪውን ያስተላልፋል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !!

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.