የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀደቀ ተባለ? By፦ Tadesse Birru K.

Standard

ህወሓትን ለማዳን ሲባል በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያዊያን ላይ የሚደረገውን ፍጅት ህጋዊ የሚያደረገው “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ” በ346 አባላት ድጋፍ፣ በ88 ተቃውሞና በ 7 ሰዎች “ከደሙ ንፁህ ነን” ድምፀ ተዓቅቦ ፀድቋል ተብሏል። እንደሚታወቀው ፓርላማው 547 መቀመጫዎች አሉት። ይህ ህግ የፀደቀው ከፓርላማው መቀመጫዎች 2/3ኛ ሳይሆን በዕለቱ ከተሰበሰቡት 2/3ኛ ስሌት መሆኑን ለትዝብት ያህል በማስገንዘብ ወደሌሎች ጉዳይ ልለፍ።

ከሁሉ አስቀድሜ የተቃወሙት 88 እና ድምፀ ተዓቅቦ ያደረጉት 7 በድምሩ 95 ሰዎች በዚህ ፓርላማ ውስጥ መገኘታቸው በኢህአዴግ አባላት ሙሉ በሙሉ ተስፋ ከመቁረጥ ታግዶናል ብዬ አምናለሁ። እነዚህን ወገኖች በተለመደ ህወሓታዊ መሰሪ “ድርጅታዊ ሥራ” ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ለማስመሰል ተቃወሙ ተብለው ታዘው እንዳልተቃወሙ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔ በዚህ ፓርላማ ውስጥ ይህን ያህል ተቃውሞ ይኖራል ብዬ አልገመትኩም ነበር። እነዚህ ወገኖች የተቃወሙት በራሳቸው ውሳኔ ከሆነ “እንኳን ደስ ያላችሁ” እላለሁ። ምንም እንኳን ዛሬ በአድርባዮች ብዛት ተሸንፋችሁ ህጉ ቢያልፍም እናንተ የተቻላችሁን አድርጋችኋልና ክብር ይገባችኋል፤ እናከብራችኋለን።

ይህ አዋጅ ለህወሓት የሚኖረው ትርጉም “በቅሎ ገመዷን በጠሰች ቢሉ በራሷ አሳጠረች” እንደተባለው ነው። አዋጁ ከሁሉም በላይ የሚጎዳው ህወሓትን ነው። አዋጁ ጮሆ የሚናገረው ህወሓት መለወጥ የማይችል በዚህም ምክንያት መጥፋት ያለበት ድርጅት መሆኑን ነው።

ከእንግዲህ ምን ይደረግ ?

1. ሕዝባዊ እምቢተኝነቶች ቀድሞ ከነበረው እጅግ በተባባሰና በተጠናከረ ሁኔታ ይቀጥሉ፤ በሕዝባዊ እምቢተኝነት ሥርዓቱ መሽመድመድ አለበት፣

2. ሕዝባዊ እምቢተኝነቶች ራስን ከጥቃት በመከላከል ተግባራት ይታጀቡ፤ ዝም ብሎ መሞት፣ መገረፍ፣ መታሰር፣ መጋዝ መቆም አለበት፣

3. በሥርዓቱ ላይ ሕዝባዊ አሻጥሮችን መሥራት የዕለት ተዕለት ኑሮዓችን አካል ይሁን፤ ከፋሽስት ህወሓት ሥርዓት ጋር መተባበር የተወገዘ ይሁን፣

4. የኅብረተሰብ ክፍሎችና የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች ኅብረቶች ይጠንክሩ፤ ነፋስ በመካከላችን አይግባ፤ የጎንዮሽ አተካራዎች ቆመው ፍላፃዎች ሁሉ ህወሓት ላይ ያነጣጥሩ፣

5. ለመከላከያ ሠራዊት አባላት ተደጋጋሚ ጥሪዎች ይደረጉ፤ አፈሙዛቸው በአለቆቻቸው ላይ እንዲያዞሩ ይበረታቱ፤ አዳዲስ ተመልማዮች እንዳይኖሩ ይደረጉ፣

6. የህወሓት ሰላዮች ሕዝብን መሰለላቸው አቁመው አለቆቻቸውን እንዲሰልሉ ይበረታቱ፣

7. ህሊና ያላቸው የኢህአዴግ አባላት ወደህሊናቸው ተመልሰው የሕዝብን ትግል እንዲያግዙ ጥረት ይደረግ፣

8. ከህወሓት በኋላ የሚመጣው ሥርዓት ለሁላችንም የምትመች ኢትዮጵያ መሆኗን የሚያረጋግጡ ሥራዎች ይሠሩ፣

9. አዋጁ የድሉን ዋጋ ከፍ ቢያደርገውም ጊዜውን ግን አቅርቦታልና ሁላችንም የየበኩላችን ተግባራዊ ተሳትፎ እናድርግ፡

Advertisements

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚቆም የነጻነት ትግል እንደማይኖር በተግባር ለማሳየት ዝግጁዎች ነን። የአርበኞች ግንቦት 7 ርዕሰ አንቀፅ

Standard

የህወሃት አገዛዝ ለዛሬ የካቲት 23 ቀን 2010 ጠርቶት የነበረው አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ የካቲት 9 ቀን 2010 የሚንስትሮች ምክር ቤት የተባለው ስብስብ ያወጀውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በ346 ድምጽ ድጋፍ በ88 ተቃውሞና በ7 ድምጸ ታዕቅቦ ማጽደቁን አስታውቆአል። ከዚህ የዛሬው የፓርላማ ውሳኔ ሁለት ነገሮችን ማስተዋል ተችሎአል።

1. ያለፈውን ምርጫ መቶ በመቶ በማሸነፍ 547ቱንም የአገሪቱን ፓርላማ መቀመጫ ሙሉ በሙሉ እንደተቆጣጠረ በኩራት ሲደሰኩርና አለምን ሲያስደምም የቆየው የህወሃት/ኢህአደግ አገዛዝ በዛሬው የፓርላማ ውሎ የድጋፍና የተቃውሞ ድምጽ የሰጡ አባላቱ ብዛት 441 ብቻ እንደሆኑ ሲያስታውቅ የተቀሩት 106 አባላቱ የት እንደደረሱ እንኳ መግለጽ አለማቻሉ የደረሰበት የውስጥ ቀውስ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለመሸፈን ከማይችልበት አጣብቂኝ ውስጥ መውደቁን ያስገነዝባል።

2. አገዛዙ እመራበታለሁ በሚለው ህገመንግሥት እንዲህ አይነት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማወጅ ከፓርላማ አባላቱ የ2/3ኛ ድምጽ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ በግልጽ ተቀምጦ እያለ እና የ547 አባላት 2/3ኛ ድምጽ ማለት ቢያንስ የ365 ሰዎች ድጋፍ ማለት መሆኑ እየታወቀ በምን ሲሌት የ346 አባላት ድጋፍ አዋጁን ለማስጸደቅ ችሎአል እንደተባለ ይዞት የመጣው ተቃርኖ ስላስጨነቀው ይመስላል ቀጥሎ ቁጥሩን ለመለዋወጥ የሚታገለውና በኮረም ሞልቷል ስም ሊያምታታ የሚሞክረው።

ወያኔ ለማናፈስ እንደሚሞክረው የአስቸካይ ጊዜ አዋጁን በፓርላማ ለማስጸደቅ ኮረም ሞላለት አልሞላለት የኢትዮያ ህዝብ በዛሬው ቀን በተካሂደው አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ተላለፈ ከተባለው ከዚህ ውሳኔ አንድ ትልቅ ድል ተቀዳጅቶአል። ይሄውም መቶ በመቶ የህወሃት/ ኢህአደግ አባላት መሆናቸው ከሚታወቅ 547 የፓርላማ አባላቱ መካከል 106ቱ ስብሰባው የተጠራበት አላማ በህዝባቸውና በወገናቸው ላይ እልቂትን ለማወጅ እንደሆነ ተረድተው የውሳኔው አካል ላለመሆን የፓርላማ ስብሰባ ላይ ላለመገኘት መወሰናቸው ፤ 88ቱ ደግሞ በታሪክና በህግ ፊት ተጠያቂ ላለመሆን አዋጁ እንዳይጸድቅ በግልጽና በድፍረት የተቃውሞ ድምጻቸውን ማስመዝገብ መቻላቸውና 7ቱ ድምጸ ተአቅቦ በማድረግ በድምሩ 201 አባላቱ ከህዝብ ጋር መወገናቸውን በተግባር ማሳየታቸው ነው ። ይህን እርምጃ የወሰዱት እነዚህ 201 የፓርላማ አባላት ሰሞኑን ቱባ ቱባ የህወሃት ካድሬዎችና የደህንነት መሥሪያቤቱ ሃላፊዎች እያንዳንዱን የኢህአደግ አባል ድርጅት አመራሮችንና የፓርላማ ተወካዮችን ከቤት ቤት እያሳደዱ በተለመደው ዘዴያቸው ከተቻለ በጥቅም በመደለል ካልሆነ ደግሞ በፍርሃት በማሽመድመድ አዋጁ እንደተለመደው በሙሉ ድምጽ እንዲያጸድቁት ሲፈጥሩባቸው የነበረውን ጫና ሁሉ በመቋቋም የወሰዱት እርምጃ እንደሆነ ይታወቃል። ለነጻነቱ እየተፋለመ ያለው ህዝባችን ይህ አፋኝ አዋጅ በፓርላማው ውስጥ ህወሃት እንደተመኘው በሙሉ ድምጽ እንዳይጸድቅ ላሰናከሉትና ሽንፈት እንዲጎነጭ ላደረጉት በተለይም ደግሞ በድፍረት የተቃውሞ ድምጻቸውን ላስመዘገቡ የፓርላማ አባላት ትልቅ አድናቆት አለው። እነዚህ ወገኖች የህዝባቸውን መከራና ሲቃይ ለማስቆም የሚችሉትን አድርገዋልና በታሪክና በህግ ፊት ብቻ ሳይሆን በወገናቸው ፊትም እራሳቸውን ከተጠያቂነት ነጻ እንዳደረጉ አውቀው ይህ አዋጅ በህዝባቸው ላይ የሚያደርሰው እልቂት እንዳይሳካ ከህዝባቸው ጎን ቆመው እስከመጨረሻው መፋለም ይጠበቅባቸዋል። እዛው ፓርላማ ውስጥ ሆነው ሊያበረክቱት የሚችሉት አስተዋጾ ቀላል እንዳልሆነ እነርሱም ህዝባችንም በሚገባ ያውቁታል። በአንጻሩ እዚያው ፓርላማ ውስጥ በወያኔ እጅ ጥምዘዛ ተሸንፈው ወይም እስከዛሬ ያገኙትን የጥቅም ፍርፋሪ እንዳይቀርባቸው አስበው ወይም ጥቅማቸውን አስልተው ይህ ፋሽስታዊ አዋጅ እንዲጸድቅ የድጋፍ ድምጻቸውን የሰጡ ወገኖች የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር በህግና በታሪክ ፊት ብቻ ሳይሆን በህዝባቸውም ዘንድ የሚጠየቁበት ቀን ሩቅ እንዳልሆነ ሊገነዘቡት ይገባል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀበት ቀን ጀምሮ ሰሞኑን በደምቢዶሎና በነቀምቴ ለፈሰሰው የንጹሃን ደም እንዲሁም ከአሁን ቦኋላ በወገኖቻችን ላይ ለሚፈጸመው ጭፍጨፋ ከህወሃት እኩል ተጠያቂ እንደሚሆኑ መዘንጋት የለባቸውም።

ህዝባችን ለመብቱና ለነጻነቱ የጀመረውን ትግል በሃይል ለመጨፍለቅ እብሪተኞቹ የህወሃት መሪዎች ያወጁት ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምንም መንገድ የታለመለትን አላማ እንዳይመታ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 አገዛዙ ካሰማራው የጸጥታ ሃይል ጋር እየተፋለመ ካለው ህዝባችን ጎን ቆሞ የሚችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ እንደሆነ ለጠላትም ለወዳጅም በፍጹም ልበ ሙሉነት ይገልጻል። ።

በዘመናዊ ጦር እስከ አፍንጫው የታጠቀውን የጠላት ጦር የዛሬ 122 አመት አድዋ ላይ አፈር ከድሜ አብልቶ ነጻነቱንና ሉአላዊነቱን አስከብሮ የኖረው ጀግኖች አባቶቻችን የልጅ ልጆች ነንና በአገር ሃብት ዘረፋ ልባቸው ያበጠው የህወሃት መሪዎች የተማመኑበት ጦር ብዛትና መሣሪያ ጋጋት ከጀመርነው የነጻነት ትግል ለአፍታም ቢሆን እንደማያስቆመን በተግባር ማሳያ ጊዜ አሁን እንደሆነ አርበኞች ግንቦት 7 አንዳቺ ጥርጣሬ የለውም ።

ግፍና መከራ በቃኝ ብለህ የተነሳሄው የኢትዮጵያ ወጣት ፤ የአገርህን ዳር ድንበር ለመጠበቅ ስትል በመከላኪያ ሠራዊት ፤ በፖሊስ ሃይልና በደህንነት ተቋማት ውስጥ በማገልገል ላይ ያለህ ከህዝብ አብራክ የወጣህ ወገናችን ! ይህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የህወሃት ዕድሜ ማራዘሚያ ሳይሆን የሚመካበት ጉልበትና አቅም መጥፊያው መሆኑን አውቆ እራሱን ለህዝብ ጥያቄ እንዲያስገዛና ሁሉንም ተቃዋሚ ሃይል ባሳተፈ የሽግግር ሂደት ህዝባችን እየተዋደቀለት ወዳለው የዲሞክራሲ ሥርዓት እንድንገባ ንቅናቄያችን አርበኞች ግንቦት 7 እያካሄደ ካለው ትግል ጎን እንድትሰለፍ ወገናዊ ጥሪ ቀርቦልሃል ።

በዚህ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ወጣት የእስከ ዛሬ ዝምታውን ሰብሮ ዛሬ በተካሄደው የአደዋ ድል በዓል ላይ ያሰማው “ይለያል ዘንድሮ የወያኔ ኖሮና እናት ኢትዮጵያ የደፈረሽ ይውደም” መፈክሮች ተጠናክሮ እንዲቀጥልና አድስ አበባችን የወያኔ እብሪትና ጥጋብ ማስተንፈሻ ማሳያ ትግል አደባባይ እንዲሆን አርበኞች ግንቦት 7 ለአዲስ አበባ ወጣት ልዩ ወገናዊ ጥሪውን ያስተላለፋል።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ !

የሞት አዋጁ ጸድቋል (በጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

Standard

ብዙዎቻችን ትንሽ ዕድል ሰጥተናቸዋል። ምናልባት የዘመናት ሃጢያታቸውን በዚህች ቆራጥ ውሳኔያቸው ሊያካክሱ ይችሉ ይሆን በሚል ግመል በመርፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ዓይነት የሚመስል ተስፋ ያሳደርን ጥቂቶች አይደለንም። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በጉልበት ለመቀጠል በሚል ያወጣውን የሞት አዋጅ ፓርላማው ተባባሪ እንዳይሆን ጥረቶች ተደርገዋል። በአብዛኛው የፓርላማ አባላት ዘንድ በስልክና በአካል በመድረስ አዋጁን በማጽደቅ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆኑ በሚገባ ተነግሯቸዋል። የድርጅት ማዕከላዊነትን በመስበር አዋጁን ውድቅ እንዲያደርጉት ተጎትጉተዋል። ተለምነዋል:: ቢቃወሙትም ባይቃወሙትም የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን የነጻነት ተጋድሎ እንደማያቆመውም በሚገባ እንዲያውቁት ተደርገዋል:: ለራሳቸው መልካም ስም ሲሉ ብቻ አዋጁን አሽቀንጥረው እንዲጥሉት ተመክረዋል::

ምንም እንኳን ከህዝብ ግፊት በተጓዳኝ የትግራይ ጀነራሎችና ደህንነቶች ማስፈራሪያ እንደነበረ ቢታወቅም በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ለየትኛውም የአገዛዙ ቁንጥጫ የማይንበረከኩ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት በግሌ ውስጤ ነበር። በመጨረሻ ግን የተጠበቀው ሆኗል። ፓርላማው ታሪክ መስራት የማይችል እንደሆነ ዳግም አስመስክሯል። የፓርላማ አባላቱ እየሰመጠ ካለው መርከብ ዘለው እንዲወርዱ የተሰጣቸውን የመጨረሻ ዕድል አልተጠቀሙበትም። አብረው መስመጥን መርጠዋል።

በእርግጥ አዋጁ በሙሉ የፓርላማ አባላት ይሁንታ የጸደቀ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከ80 በላይ አባላት የሞት አዋጁን መቃወማቸው ይነገራል። ይሄ በራሱ የሚነገረን የድርጅት ማዕከላዊነት መሰበሩን ነው። ወይም ደግሞ በጫናና ማስፈራራት ሳይሆን በነጻነት የተካሄደ የድምጽ አሰጣጥ ተደርጎ እንዲወሰድ በትግራዩ አገዛዝ በኩል የተጻፈ ድርሰት ሊሆን ይችላል። የፓርላማውን ቁልፍልፍ አሰራርና የትግራዩ አገዛዝ የሚጎነጉነውን ሴራ በቅርበት የሚያውቁት አስምረው የሚናገሩት አዋጁ ማዕከላዊነትን በጠበቀ አካሄድ በሙሉ ድምጽ የመጽደቅ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ነው።

እያንዳንዱ አባል የያዘው ድምጽ የግሉ አይደለም። የወከለው ፓርቲ ነው። ፓርቲው የወሰነውን አባሉ በፓርላማ እጁን አውጥቶ እንዲጸድቅ ከማድረግ ያለፈ ምንም ስልጣን የለውም። የፓርላማ አባሉ ውክልናው ለመረጠው ህዝብ ሳይሆን ላስመረጠው ድርጅቱ ነው። ይህ የትግራዩ አገዛዝ ፓርላማውን ያዋቀረበት ውስጣዊ አሰራር ነው። ፍጹም ነጻነትን የሚነጥቅ ስታሊናዊ አሰራር ነው። ይህ አሰራር ነው ላለፉት 27 ዓመታት የትግራዩን አገዛዝ በህግ ሽፋን ሀገሪቱን እንዳሻው እንዲጫወትባት ያደረገው።

ዛሬ በሞት አዋጁ ላይ ድርጅታዊ ማዕከላዊነት እንዳልነበረ የሚያሳይ የድምጽ ውጤት ተመዝግቧል። ከ80 በላይ የሚሆኑ አዋጁን ከተቃወሙት ውሳኔው የድርጅትን መስመር ተከትሎ የተካሄደ ነው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም። እነዚህ 80ዎቹ ለምን ተነጥለው አዋጁን ተቃወሙት? ማዕከላዊነት ተሰበረ ወይስ በሀሳብ ፍጭት፡ በነጻነት የተደረገ የድምጽ አሰጣጥ ነው የሚል ድራማ ተሰርቶ ይሆን?

ምንም ሆነ ምን አዋጁ ጸድቋል። አሳፋሪው ታሪክ ተመዝግቧል። ፓርላማው ዕድሉን አጨናግፏል። በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ ላይ የታወጀን ጦርነት ያጸደቀ ፓርላማ ከሚል ጥቁር መገለጫ ጋር የሚነሳ ፓርላማ ሆኗል። ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። አዋጁን አጥብቆ ሲያወግዝ የነበረው የኦህዴድ-ለማ ቡድን ከእንግዲህ ምን ሊያደርግ ይችላል? የትግራዩን አገዛዝ ለማዳን ህዝባቸውን የካዱት እነአባዱላ ገመዳ በአሸናፊነት የኦህዴድን መሪ ይጨብጡ ይሆን? ውጭ ያሉት የኦሮሞ አክቲቪስቶች የፓርላማውን ውሳኔ እየጠበቅን ነው– ከጸደቀ መሬት አንቀጥቅጥ አድማ እንዲጠራ እንቀሰቅሳለን ያሉትን ቃላቸውን ያጥፉ ይሆን? የዛሬው የፓርላማ ውሳኔ የተበታተነውን ትግል በአንድ ቋት ውስጥ አስገብቶ ለስርነቀል ለውጥ ያነሳሳልን?

ከፀፀት ለመዳን ነገ ”አይሆንም“ ድምጽ መስጠት ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርላማ አባል መሆን እንደ አሁን ሰቆቃ የሆነበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም። (በዶ/ር ታደሰ ብሩ)

Standard

የፓርላማ አባላት ድምጽ ሲሰጡ ”የመረጣቸውን ሕዝብ“ እና ህሊናቸውን አዳምጠው ሳይሆን “ጠርናፊያቸው” ባዘዘው መሠረት መሆኑ መቸም ቢሆን ምቾች የሚሰጥ ነገር ባይሆንም ነገ እንደምናየው አሸማቃቂ ጉዳይ አልነበረም። “በጠርናፊ ትዕዛዝ” ድምጽ መስጠት ነገ በዚህ ሰዓት በብዙዎች ህሊና ውስጥ የሚያደርሰውን መሸማቀቅ ያህል ያደርስ ነበር ብዬ አላስብም።

የነገው መሸማቀቅ ከእስከ ዛሬው ሁሉ ይለያል። ነገ ህግ ሆኖ እንዲያልፍ የይሁንታ ድምጽ የሚሰጡለት አዋጅ ሳሞራ የኑስንና ጌታቸው አሰፋን ከፓርላማው በላይ የሚያደርግ፤ የሳሞራና ጌታቸው ሎሌዎች በዜጎች ላይ ለሚያደርሱት ፍጅት ሽፋንና ከለላ የሚሰጥ ህግ መሆኑን ህሊናቸው ስለሚረዳ ድምጽ ሰጥተው ከአዳራሹ ሲወጡ የሚደርስባቸው ውስጣዊ መሸማቀቅ ይታየኛል። የፓርላማው አባላት ነገ የሚያፀድቁት ህግ አንድ ፋሽስታዊ ቡድን መላውን የመንግሥት መዋቅር እንዲቆጣጠር በድምጽ ብልጫ በይፋ የወሰኑበት ቀን ሆኖ ይመዘገባል። ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በመዋሉ ምክንያት ዜጎች እየተገደሉ ነው፤ ድጋፋቸውን ሰጥተው ካፀደቁበት ደቂቃ ጀምሮ በርካታ ዜጎች ይገደላሉ፣ ይገረፋሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ። ችግሮች ሳይፈቱ ግልጽ ሁከቶችን ብቻ በማስወገድ ወይን በማፈን የሚገኝ አሉታዊ ሰላም ዘላቂ እንዳልሆነ እንዲያው እጅግ አደገኛ መዘዝ እንዳለው ልቦናዎቻቸው ይነግሯቸዋል።

ለዚህ አዋጅ የድጋፍ ድምጽ መስጠት ከራስ አልፎ ለልጅ ልጆች የሚተርፍ ፀፀት ነው። ከዚህ ፀፀት መዳን የሚቻለው የሚያስከፍለው ዋጋ በጀግንነት ተቀብሎ ”አይሆንም“ የሚል ድምጽ መስጠት ነው። በነገው ዕለት የሚሰጥ የአንድ ሰው እንኳን “አይሆንም” ድምጽ ከፍተኛ ዋጋ አለው፤ ያ ሰው ከገዳዮቻችን አንዱ አይደለም።

ከቄሮ የተላለፈ ማስታወቂያ

Standard

በምእራብ ኦሮሚያ እየተፈፀመ ባለው ግድያ እና በዛሬው ዕለትም ለሠራዊቱ ሕዝባችንን እንዲገድል በተሰጠው ግልፅ ትእዛዝ ሃገሪቱ ወደ አደገኛ ሁኔታ እያሽቆልቆልች ነው። የፓርላማ አባላት በ አስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁ ላይ አቋም እስኪወስዱና አስኪያግዱት ወይም እስኪያፀድቁት ቄሮ የራሱን ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል። የፓርላማ አባላት የፊታችን አርብ በሚደረገው የፓርላማ ስብሰባ የ አስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁን እንዲያፀድቁ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን እያስፈራራቸው እንደሆነ እየሰማን ነው። ፓርላማው ይህን ሕገ ወጥ የ አስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ የሚያፀድቀው ከሆነ በቁርጠኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዲቀለበስ ይደረጋል። በመሆኑም ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግም ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊደርግ የታሰበ ጉዞ በሙሉ ከፊታችን አርብ ጀምሮ ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም አበክረን እናሳስባለን።

‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሻሚ ቋንቋና ሰፊ ክልከላዎችን የያዘ ነው” ሂዩማን ራይትስ ዋች

Standard

በቅርቡ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቦታ የበለጠ ሊያጠበው እንደሚችል ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

ሪፖርቱ ጨምሮ እንዳለው መንግሥት በዓለም አቀፍ ሕጎች ጥበቃ የሚደረግላቸውን በነፃነት የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሃሳብን የመግለፅ መብቶችን የሚከለክለውን ይህንን አዋጅ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ወይም እንዲያሻሽል ጠይቋል።

ሪፖርቱ ቀደም ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ከ20ሺህ በላይ ሰዎችን ማሰራቸውንና መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን አስታውሷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌውን የሚተቹ የሚባሉ መረጃዎችን ማሰራጨት የሚከለክል ከመሆኑ በተጨማሪ የአዋጁን አፈፃፀም የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት መገናኛ ብዙሃንን ለመዝጋት የሚያስችል ስልጣን ተሸጥቶታል።

ይህም በኢትዮጵያ ያሉት መገናኛ ብዙሃንና እየሰፋ የመጣውን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ላይ አሳሳቢ ስጋት የሚደቅን ነው ብሏል ሪፖረቱ።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ በኋላ በመከላከያ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሻሚ ቋንቋና ሰፊ ክልከላዎችን የያዘ መሆኑን የገለፀው የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት፤ ይህ ሁኔታ መንግሥት ለሚወስዳቸው ያልተገቡ እርምጃዎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል ብሏል።

አብዛኛዎቹ የመመሪያው ቋንቋዎች ግልፅ አይደሉም። በርካታ ቃላት ትርጉማቸው አልተቀመጠም።ለምሳሌ ‘ከፀረ ሰላም ቡድኖች ጋር መገናኘት’ ወይም ‘መቻቻልንና አንድነትን የሚያውክ’ ተግባርን ከመፈፀም መቆጠብ ይገኝበታል።

መንግሥት ሰላማዊ ጥያቄዎችን በሃይል በሚመልስበት የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ፤ እነዚህ ግልፅ ያልሆኑ አንቀፆች የፀጥታ ኃይሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መጣስ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን እንዳሻቸው እንዲወስኑ ገደብ የለሽ ስልጣን ይሰጣቸዋል ብሏል ሪፖርቱ።

ሌላው ችግር ያለበት የፀጥታ ሃይሎች አመፅን ለማስቆም ያልምንም ፍቃድ ትምህርትቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡና እንዲያስሩ የሚፈቅደው አንቀፅ ነው።

ይህ አንቀፅ መኖሪያ ቤቶችን ያለምንም ፍቃድ እንዲፈትሹም ለፀጥታ ሃይሎች የሚፈቅድ ሲሆን ከቤት ያለመውጣት አድማን፣ንግድ ቤትን አለመክፈትን፣ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ ሰላማዊ ተቃውሞን ይከለክላል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው ያለ ኮማንድ ፖስቱ ትእዛዝ ሊታሰርና ሊከሰስ ይችላል። ተሃድሶ እንዲወስድም ይደረጋል። ክስ ሳይመሰረት በእስር ማቆየት የመብት ጥሰቶችና በፖለቲካ አመለካከት ማጥመቅ የሚስተዋልበት ነው። ስቃይና ያልተገባ እስረኛ አያያዝ በኢትዮጵያ ትልቅ ችግሮች ናቸው እንደሆነ ሂዩማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ አመልክቷል።

በነቀምት ውጥረቱ ተባብሶ ቀጥሏል

Standard

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 20/2010) በነቀምት ውጥረቱ ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ። ዛሬ ጠዋት አንድ ወጣት በአልሞ ተኳሽ ወታደር መገደሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጂን በመጣስ ተቃውሞ እያደረጉ ባሉ የነቀምት ነዋሪዎች ላይ ተኩስ የከፈቱት የአገዛዙ ወታደሮች ከ20 በላይ ሰዎች ማቁሰላቸውም ታውቋል። ቤት ለቤት አፈሳ የተጀመረ መሆኑኑም ተመልክቷል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ አመራሮች በወለጋ ደጋፊዎቻቸውን ለማግኘት ቀጠሮ የያዙት ከአስቸኳይ አዋጁ ይፋ መሆን ቀደም ብሎ ነበረ። አመራሮቹ መርሃ ግብራቸውን ጠብቀው በየከተሞቹ እየተገኙ ደጋፊዎቻቸውን ሲያነጋግሩ ቆይተው ወደ ነቀምት ያመራሉ። ነቀምት ለመድረስ 5 ኪሎ ሜትር ሲቀራቸው በኮማንድ ፖስቱ መታገታቸውን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። የነቀምትን ስታዲየም ሞልቶ የሚጠብቃቸው ህዝብ ዜናውን ሲሰማ ወዲያኑ የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት መጀመሩ በወቅቱ ተገልጿል። አስቸኳይ አዋጁ ስለሚከለክል ህዝብ መሰብሰብ አትችሉም የተባሉት የኦፌኮ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ነቀምት በተቃውሞ ተናወጠች። መንገዶች በተቃጠሉ ጎማዎች ተሞሉ። አገዛዙ ከስልጣን እንዲወርድ የሚጠይቁ መልዕክቶች አደባባይ በወጣው ህዝብ መስተጋባት ጀመሩ። ትላንት መሀል ነቀምት የጦርነት ቀጠና ይመስል ነበር። (ድምጽና ቪዲዮ) ከመሪዎቻቸው ጋር እንዳይገናኙ የተደረጉት የነቀምቴ ነዋሪዎች በአስቸኳይ አዋጅ ውስጥ ሆነውም ተቃውሞአቸውን ቀጥለዋል። ዛሬም ህዝብ ጸረ መንግስት መልዕክቶችን ሲይሰማ እንደነበረ ታውቋል። በተለይ ዛሬ ጠዋት በዋና ዋና የነቀምት አውራ ጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንድነበረ ተገልጿል። ከቀትር በኋላ ግን ከተማዋን የአገዛዙ ታጣቂዎች መውረራቸውን ከአከባቢው የመጣው ዜና ያስረዳል። የአንድ ወጣት ግድያን ተከትሎ ነቀምት ሙሉ በሙሉ በአገዛዙ ወታደሮች ቁጥጥር ስር መውደቋ ታውቋል። በመሃል ነቀምት አደባባይ ላይ በአልሞ ተኳሽ ጥይት የተገደለው ወጣት አበበ መኮንን የሚባል እንደሆነ ተገልጿል። ወጣት አበበ ከተገደለ በኋላ ለበርካታ ሰዓታት አስክሬኑ አደባባይ ላይ እንዲቆይ ተደርጓል። ከትላንት ጀምሮ በአገዛዙ ወታደሮች በተወሰደ እርምጃ ከ20 በላይ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል። ከኦፌኮ አመራሮች የወለጋ ጉዞ ጋር በተያያዘ በተነሳ ተቃውሞ የሰው ህይወት ሲጠፋ የዛሬ ሁለተኛው ሲሆን ባለፈው ቅዳሜም በደምቢዶሎ አንድ ሰው መገደሉ ሲታወስ ፡ሰባት ቆስለዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ተቃውሞውን በቀጠለው የነቀምት ነዋሪ ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ በኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተከትሎ በነቀምት ውጥረት ነግሷል። ለጊዜው ቁጥሩ ባይታወቅም በርካታ ሰዎች መታፈሳቸው ታውቋል። የከተማዋ እንቅስቃሴ የተቋረጠ ሲሆን በመንገዶች ላይ የሚታዩት የአገዛዙ ወታደሮች ብቻ መሆናቸውን በቪዲዮ ተደግፎ ከወጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።