የሞት አዋጁ ጸድቋል (በጋዜጠኛ መሳይ መኮንን)

Standard

ብዙዎቻችን ትንሽ ዕድል ሰጥተናቸዋል። ምናልባት የዘመናት ሃጢያታቸውን በዚህች ቆራጥ ውሳኔያቸው ሊያካክሱ ይችሉ ይሆን በሚል ግመል በመርፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ዓይነት የሚመስል ተስፋ ያሳደርን ጥቂቶች አይደለንም። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በጉልበት ለመቀጠል በሚል ያወጣውን የሞት አዋጅ ፓርላማው ተባባሪ እንዳይሆን ጥረቶች ተደርገዋል። በአብዛኛው የፓርላማ አባላት ዘንድ በስልክና በአካል በመድረስ አዋጁን በማጽደቅ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆኑ በሚገባ ተነግሯቸዋል። የድርጅት ማዕከላዊነትን በመስበር አዋጁን ውድቅ እንዲያደርጉት ተጎትጉተዋል። ተለምነዋል:: ቢቃወሙትም ባይቃወሙትም የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረውን የነጻነት ተጋድሎ እንደማያቆመውም በሚገባ እንዲያውቁት ተደርገዋል:: ለራሳቸው መልካም ስም ሲሉ ብቻ አዋጁን አሽቀንጥረው እንዲጥሉት ተመክረዋል::

ምንም እንኳን ከህዝብ ግፊት በተጓዳኝ የትግራይ ጀነራሎችና ደህንነቶች ማስፈራሪያ እንደነበረ ቢታወቅም በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ለየትኛውም የአገዛዙ ቁንጥጫ የማይንበረከኩ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት በግሌ ውስጤ ነበር። በመጨረሻ ግን የተጠበቀው ሆኗል። ፓርላማው ታሪክ መስራት የማይችል እንደሆነ ዳግም አስመስክሯል። የፓርላማ አባላቱ እየሰመጠ ካለው መርከብ ዘለው እንዲወርዱ የተሰጣቸውን የመጨረሻ ዕድል አልተጠቀሙበትም። አብረው መስመጥን መርጠዋል።

በእርግጥ አዋጁ በሙሉ የፓርላማ አባላት ይሁንታ የጸደቀ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከ80 በላይ አባላት የሞት አዋጁን መቃወማቸው ይነገራል። ይሄ በራሱ የሚነገረን የድርጅት ማዕከላዊነት መሰበሩን ነው። ወይም ደግሞ በጫናና ማስፈራራት ሳይሆን በነጻነት የተካሄደ የድምጽ አሰጣጥ ተደርጎ እንዲወሰድ በትግራዩ አገዛዝ በኩል የተጻፈ ድርሰት ሊሆን ይችላል። የፓርላማውን ቁልፍልፍ አሰራርና የትግራዩ አገዛዝ የሚጎነጉነውን ሴራ በቅርበት የሚያውቁት አስምረው የሚናገሩት አዋጁ ማዕከላዊነትን በጠበቀ አካሄድ በሙሉ ድምጽ የመጽደቅ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ነው።

እያንዳንዱ አባል የያዘው ድምጽ የግሉ አይደለም። የወከለው ፓርቲ ነው። ፓርቲው የወሰነውን አባሉ በፓርላማ እጁን አውጥቶ እንዲጸድቅ ከማድረግ ያለፈ ምንም ስልጣን የለውም። የፓርላማ አባሉ ውክልናው ለመረጠው ህዝብ ሳይሆን ላስመረጠው ድርጅቱ ነው። ይህ የትግራዩ አገዛዝ ፓርላማውን ያዋቀረበት ውስጣዊ አሰራር ነው። ፍጹም ነጻነትን የሚነጥቅ ስታሊናዊ አሰራር ነው። ይህ አሰራር ነው ላለፉት 27 ዓመታት የትግራዩን አገዛዝ በህግ ሽፋን ሀገሪቱን እንዳሻው እንዲጫወትባት ያደረገው።

ዛሬ በሞት አዋጁ ላይ ድርጅታዊ ማዕከላዊነት እንዳልነበረ የሚያሳይ የድምጽ ውጤት ተመዝግቧል። ከ80 በላይ የሚሆኑ አዋጁን ከተቃወሙት ውሳኔው የድርጅትን መስመር ተከትሎ የተካሄደ ነው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም። እነዚህ 80ዎቹ ለምን ተነጥለው አዋጁን ተቃወሙት? ማዕከላዊነት ተሰበረ ወይስ በሀሳብ ፍጭት፡ በነጻነት የተደረገ የድምጽ አሰጣጥ ነው የሚል ድራማ ተሰርቶ ይሆን?

ምንም ሆነ ምን አዋጁ ጸድቋል። አሳፋሪው ታሪክ ተመዝግቧል። ፓርላማው ዕድሉን አጨናግፏል። በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ ላይ የታወጀን ጦርነት ያጸደቀ ፓርላማ ከሚል ጥቁር መገለጫ ጋር የሚነሳ ፓርላማ ሆኗል። ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። አዋጁን አጥብቆ ሲያወግዝ የነበረው የኦህዴድ-ለማ ቡድን ከእንግዲህ ምን ሊያደርግ ይችላል? የትግራዩን አገዛዝ ለማዳን ህዝባቸውን የካዱት እነአባዱላ ገመዳ በአሸናፊነት የኦህዴድን መሪ ይጨብጡ ይሆን? ውጭ ያሉት የኦሮሞ አክቲቪስቶች የፓርላማውን ውሳኔ እየጠበቅን ነው– ከጸደቀ መሬት አንቀጥቅጥ አድማ እንዲጠራ እንቀሰቅሳለን ያሉትን ቃላቸውን ያጥፉ ይሆን? የዛሬው የፓርላማ ውሳኔ የተበታተነውን ትግል በአንድ ቋት ውስጥ አስገብቶ ለስርነቀል ለውጥ ያነሳሳልን?

Advertisements

ከፀፀት ለመዳን ነገ ”አይሆንም“ ድምጽ መስጠት ኢትዮጵያ ውስጥ የፓርላማ አባል መሆን እንደ አሁን ሰቆቃ የሆነበት ጊዜ ያለ አይመስለኝም። (በዶ/ር ታደሰ ብሩ)

Standard

የፓርላማ አባላት ድምጽ ሲሰጡ ”የመረጣቸውን ሕዝብ“ እና ህሊናቸውን አዳምጠው ሳይሆን “ጠርናፊያቸው” ባዘዘው መሠረት መሆኑ መቸም ቢሆን ምቾች የሚሰጥ ነገር ባይሆንም ነገ እንደምናየው አሸማቃቂ ጉዳይ አልነበረም። “በጠርናፊ ትዕዛዝ” ድምጽ መስጠት ነገ በዚህ ሰዓት በብዙዎች ህሊና ውስጥ የሚያደርሰውን መሸማቀቅ ያህል ያደርስ ነበር ብዬ አላስብም።

የነገው መሸማቀቅ ከእስከ ዛሬው ሁሉ ይለያል። ነገ ህግ ሆኖ እንዲያልፍ የይሁንታ ድምጽ የሚሰጡለት አዋጅ ሳሞራ የኑስንና ጌታቸው አሰፋን ከፓርላማው በላይ የሚያደርግ፤ የሳሞራና ጌታቸው ሎሌዎች በዜጎች ላይ ለሚያደርሱት ፍጅት ሽፋንና ከለላ የሚሰጥ ህግ መሆኑን ህሊናቸው ስለሚረዳ ድምጽ ሰጥተው ከአዳራሹ ሲወጡ የሚደርስባቸው ውስጣዊ መሸማቀቅ ይታየኛል። የፓርላማው አባላት ነገ የሚያፀድቁት ህግ አንድ ፋሽስታዊ ቡድን መላውን የመንግሥት መዋቅር እንዲቆጣጠር በድምጽ ብልጫ በይፋ የወሰኑበት ቀን ሆኖ ይመዘገባል። ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በመዋሉ ምክንያት ዜጎች እየተገደሉ ነው፤ ድጋፋቸውን ሰጥተው ካፀደቁበት ደቂቃ ጀምሮ በርካታ ዜጎች ይገደላሉ፣ ይገረፋሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰደዳሉ። ችግሮች ሳይፈቱ ግልጽ ሁከቶችን ብቻ በማስወገድ ወይን በማፈን የሚገኝ አሉታዊ ሰላም ዘላቂ እንዳልሆነ እንዲያው እጅግ አደገኛ መዘዝ እንዳለው ልቦናዎቻቸው ይነግሯቸዋል።

ለዚህ አዋጅ የድጋፍ ድምጽ መስጠት ከራስ አልፎ ለልጅ ልጆች የሚተርፍ ፀፀት ነው። ከዚህ ፀፀት መዳን የሚቻለው የሚያስከፍለው ዋጋ በጀግንነት ተቀብሎ ”አይሆንም“ የሚል ድምጽ መስጠት ነው። በነገው ዕለት የሚሰጥ የአንድ ሰው እንኳን “አይሆንም” ድምጽ ከፍተኛ ዋጋ አለው፤ ያ ሰው ከገዳዮቻችን አንዱ አይደለም።

ከቄሮ የተላለፈ ማስታወቂያ

Standard

በምእራብ ኦሮሚያ እየተፈፀመ ባለው ግድያ እና በዛሬው ዕለትም ለሠራዊቱ ሕዝባችንን እንዲገድል በተሰጠው ግልፅ ትእዛዝ ሃገሪቱ ወደ አደገኛ ሁኔታ እያሽቆልቆልች ነው። የፓርላማ አባላት በ አስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁ ላይ አቋም እስኪወስዱና አስኪያግዱት ወይም እስኪያፀድቁት ቄሮ የራሱን ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል። የፓርላማ አባላት የፊታችን አርብ በሚደረገው የፓርላማ ስብሰባ የ አስቸኩዋይ ጊዜ አዋጁን እንዲያፀድቁ በስልጣን ላይ ያለው ቡድን እያስፈራራቸው እንደሆነ እየሰማን ነው። ፓርላማው ይህን ሕገ ወጥ የ አስቸኩዋይ ጊዜ አዋጅ የሚያፀድቀው ከሆነ በቁርጠኛ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንዲቀለበስ ይደረጋል። በመሆኑም ወደ ኢትዮጵያ የሚደረግም ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ሊደርግ የታሰበ ጉዞ በሙሉ ከፊታችን አርብ ጀምሮ ሁኔታዎች እስኪረጋጉ ድረስ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም አበክረን እናሳስባለን።

‘የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሻሚ ቋንቋና ሰፊ ክልከላዎችን የያዘ ነው” ሂዩማን ራይትስ ዋች

Standard

በቅርቡ የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ቦታ የበለጠ ሊያጠበው እንደሚችል ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት አስታወቀ።

ሪፖርቱ ጨምሮ እንዳለው መንግሥት በዓለም አቀፍ ሕጎች ጥበቃ የሚደረግላቸውን በነፃነት የመሰብሰብ፣ የመደራጀትና ሃሳብን የመግለፅ መብቶችን የሚከለክለውን ይህንን አዋጅ በአስቸኳይ እንዲያነሳ ወይም እንዲያሻሽል ጠይቋል።

ሪፖርቱ ቀደም ባለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወቅት የፀጥታ ኃይሎች ከ20ሺህ በላይ ሰዎችን ማሰራቸውንና መጠነ ሰፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን አስታውሷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ድንጋጌውን የሚተቹ የሚባሉ መረጃዎችን ማሰራጨት የሚከለክል ከመሆኑ በተጨማሪ የአዋጁን አፈፃፀም የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት መገናኛ ብዙሃንን ለመዝጋት የሚያስችል ስልጣን ተሸጥቶታል።

ይህም በኢትዮጵያ ያሉት መገናኛ ብዙሃንና እየሰፋ የመጣውን የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ላይ አሳሳቢ ስጋት የሚደቅን ነው ብሏል ሪፖረቱ።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄ በኋላ በመከላከያ ሚኒስትሩ ይፋ የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሻሚ ቋንቋና ሰፊ ክልከላዎችን የያዘ መሆኑን የገለፀው የሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርት፤ ይህ ሁኔታ መንግሥት ለሚወስዳቸው ያልተገቡ እርምጃዎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል ብሏል።

አብዛኛዎቹ የመመሪያው ቋንቋዎች ግልፅ አይደሉም። በርካታ ቃላት ትርጉማቸው አልተቀመጠም።ለምሳሌ ‘ከፀረ ሰላም ቡድኖች ጋር መገናኘት’ ወይም ‘መቻቻልንና አንድነትን የሚያውክ’ ተግባርን ከመፈፀም መቆጠብ ይገኝበታል።

መንግሥት ሰላማዊ ጥያቄዎችን በሃይል በሚመልስበት የኢትዮጵያ ነባራዊ የፖለቲካ ሁኔታ፤ እነዚህ ግልፅ ያልሆኑ አንቀፆች የፀጥታ ኃይሎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መጣስ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን እንዳሻቸው እንዲወስኑ ገደብ የለሽ ስልጣን ይሰጣቸዋል ብሏል ሪፖርቱ።

ሌላው ችግር ያለበት የፀጥታ ሃይሎች አመፅን ለማስቆም ያልምንም ፍቃድ ትምህርትቤቶችና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲገቡና እንዲያስሩ የሚፈቅደው አንቀፅ ነው።

ይህ አንቀፅ መኖሪያ ቤቶችን ያለምንም ፍቃድ እንዲፈትሹም ለፀጥታ ሃይሎች የሚፈቅድ ሲሆን ከቤት ያለመውጣት አድማን፣ንግድ ቤትን አለመክፈትን፣ መንገድ መዝጋትን ጨምሮ ሰላማዊ ተቃውሞን ይከለክላል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ሰው ያለ ኮማንድ ፖስቱ ትእዛዝ ሊታሰርና ሊከሰስ ይችላል። ተሃድሶ እንዲወስድም ይደረጋል። ክስ ሳይመሰረት በእስር ማቆየት የመብት ጥሰቶችና በፖለቲካ አመለካከት ማጥመቅ የሚስተዋልበት ነው። ስቃይና ያልተገባ እስረኛ አያያዝ በኢትዮጵያ ትልቅ ችግሮች ናቸው እንደሆነ ሂዩማን ራይትስ ዋች በሪፖርቱ አመልክቷል።

በነቀምት ውጥረቱ ተባብሶ ቀጥሏል

Standard

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 20/2010) በነቀምት ውጥረቱ ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ። ዛሬ ጠዋት አንድ ወጣት በአልሞ ተኳሽ ወታደር መገደሉን የደረሰን መረጃ አመልክቷል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጂን በመጣስ ተቃውሞ እያደረጉ ባሉ የነቀምት ነዋሪዎች ላይ ተኩስ የከፈቱት የአገዛዙ ወታደሮች ከ20 በላይ ሰዎች ማቁሰላቸውም ታውቋል። ቤት ለቤት አፈሳ የተጀመረ መሆኑኑም ተመልክቷል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ኦፌኮ አመራሮች በወለጋ ደጋፊዎቻቸውን ለማግኘት ቀጠሮ የያዙት ከአስቸኳይ አዋጁ ይፋ መሆን ቀደም ብሎ ነበረ። አመራሮቹ መርሃ ግብራቸውን ጠብቀው በየከተሞቹ እየተገኙ ደጋፊዎቻቸውን ሲያነጋግሩ ቆይተው ወደ ነቀምት ያመራሉ። ነቀምት ለመድረስ 5 ኪሎ ሜትር ሲቀራቸው በኮማንድ ፖስቱ መታገታቸውን ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። የነቀምትን ስታዲየም ሞልቶ የሚጠብቃቸው ህዝብ ዜናውን ሲሰማ ወዲያኑ የተቃውሞ ድምጽ ማሰማት መጀመሩ በወቅቱ ተገልጿል። አስቸኳይ አዋጁ ስለሚከለክል ህዝብ መሰብሰብ አትችሉም የተባሉት የኦፌኮ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ነቀምት በተቃውሞ ተናወጠች። መንገዶች በተቃጠሉ ጎማዎች ተሞሉ። አገዛዙ ከስልጣን እንዲወርድ የሚጠይቁ መልዕክቶች አደባባይ በወጣው ህዝብ መስተጋባት ጀመሩ። ትላንት መሀል ነቀምት የጦርነት ቀጠና ይመስል ነበር። (ድምጽና ቪዲዮ) ከመሪዎቻቸው ጋር እንዳይገናኙ የተደረጉት የነቀምቴ ነዋሪዎች በአስቸኳይ አዋጅ ውስጥ ሆነውም ተቃውሞአቸውን ቀጥለዋል። ዛሬም ህዝብ ጸረ መንግስት መልዕክቶችን ሲይሰማ እንደነበረ ታውቋል። በተለይ ዛሬ ጠዋት በዋና ዋና የነቀምት አውራ ጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እንድነበረ ተገልጿል። ከቀትር በኋላ ግን ከተማዋን የአገዛዙ ታጣቂዎች መውረራቸውን ከአከባቢው የመጣው ዜና ያስረዳል። የአንድ ወጣት ግድያን ተከትሎ ነቀምት ሙሉ በሙሉ በአገዛዙ ወታደሮች ቁጥጥር ስር መውደቋ ታውቋል። በመሃል ነቀምት አደባባይ ላይ በአልሞ ተኳሽ ጥይት የተገደለው ወጣት አበበ መኮንን የሚባል እንደሆነ ተገልጿል። ወጣት አበበ ከተገደለ በኋላ ለበርካታ ሰዓታት አስክሬኑ አደባባይ ላይ እንዲቆይ ተደርጓል። ከትላንት ጀምሮ በአገዛዙ ወታደሮች በተወሰደ እርምጃ ከ20 በላይ ሰዎች ቆስለው ሆስፒታል ገብተዋል። ከኦፌኮ አመራሮች የወለጋ ጉዞ ጋር በተያያዘ በተነሳ ተቃውሞ የሰው ህይወት ሲጠፋ የዛሬ ሁለተኛው ሲሆን ባለፈው ቅዳሜም በደምቢዶሎ አንድ ሰው መገደሉ ሲታወስ ፡ሰባት ቆስለዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በመጣስ ተቃውሞውን በቀጠለው የነቀምት ነዋሪ ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ በኮማንድ ፖስቱ ትዕዛዝ መሰጠቱን ተከትሎ በነቀምት ውጥረት ነግሷል። ለጊዜው ቁጥሩ ባይታወቅም በርካታ ሰዎች መታፈሳቸው ታውቋል። የከተማዋ እንቅስቃሴ የተቋረጠ ሲሆን በመንገዶች ላይ የሚታዩት የአገዛዙ ወታደሮች ብቻ መሆናቸውን በቪዲዮ ተደግፎ ከወጣው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።

የተፈቱት እስረኞች ከአሜሪካ ኤምባሲ ሃላፊዎች ጋር ተገናኙ!

Standard

ዛሬ የካቲት 19/2010 የአሜሪካ ኢምባሲ በራዲሰን ሆቴል ለአንዱአለምና አራጌና ለእስክንድር ነጋ የምሳ ግብዣ አደረገላቸው!!

በዚህ የምሳ ግብዣ ላይ ከአሜሪካ ሀገር ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሶስት (3) ሰዎች አንዱአለምንና እስክንድር ያናገሩዋቸው ሲሆን፣ አንደኛዋ ሜሪላንድ ውስጥ ካምብሪጅ የምትባል ከተማ ከንቲባ መሆናቸው ታውቋል። ሁለቱ ግለሰቦች ደግሞ አክቪስቶች ናቸው። በውይይታቸው፣ በብሄራዊ እርቅ ዙሪያ ሰፊ ውይይት ማድረጋቸውን ከስፍራው የደረሰኝ ዜና ያስረዳል።

ችግሮችን በሰላማዊ መንገድና በውይይት መፍታት እንደሚያስልፈግ መነጋገራቸውንና፣ በዚህ ንግግር ላይ ከኢምባሲው ባለስልጣናት የተወከሉ ተጨማሪ ሶስት ሰዎች መገኘታቸው ታውቋል። ሶስቱ ሃላፊዎች የፖለቲካ ክፍልና የፕሬስ ክፍል ባለስልጣናት ሲሆኑ፣በቀጣይም ከኢምባሲው ካሉ ኅላፊዎች ጋር ተጨማሪ ንግግር ለማድረግ ቀጠሮ ይዘው መለያየታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

ግልፅ ደብዳቤ ከቄሮ “ክፍት ደብዳቤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሙሉ” ከኦሮሞ ቄሮ የተላለፈ ጥሪ

Standard

ከሁሉም አስቀድመን ባላችሁበት ሰላምታ ይድረሳችሁ።

ሁላችንም እንደሚናውቀው የኦሮሞ ቄሮዎች ህይውታችንን መስዋዕት አዲርገን የኦሮሞ ህዝብ መብትና ብሄርቤረሰቦች እኩልነት የተረገጋጠባትን ኢትዮጽያ ለመመስረት ሰላማዊ ትግል እያደረግን ነው። የኦሮሞ ህዝብ ሰላማዊ ትግል ይህችን አገር እየቀየራት ይገኛል።

ይሁን እንጅ አንባገነን የሆኑ የTPLF ጥቂት ኮንትሮባንዲስቶች ቡድን አገሪቷን ለማዝረፍ በተሃድሶ መሪዎች ና በቄሮ የተዘጋባቸዉን የዝርፍያ መንገድ መልሰዉ ለመቆጣጠር ፣ አገርቷን በጦር ሀይል ለማቆጠጣር አስቻኳይ ግዜ አወጅ እያዋጁ ይገኛሉ። ይሄ አዋጅ በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት አይኖረዉም።

የተከበራችሁ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኮንትሮባንድስቶች አገሪቷን ለመበዝበዝ እና ለመበታተን በኦሮሞ ህዝብና በመላው ብሄርቤረሰቦች ላይ የታዋጀ አዋጅ እንዲሰረዝ የበኩላችሁን የዜግነት ግደታ በመወጣት አገሪቷን ከዉድቀት እና ከመበታተን እንድታድኑ የኦሮሞ ቄሮ በዚህ ደብዳቤ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

ከዚህ እልፎ አዋጁ የሚጸድቅ ከሆነ የኦሮሞ ቄሮና ህዝብ የአፀፋ ምላሽ ተጠያቂዎቹ TPLF ና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት መሆናችሁን እናሳስባለን።

ከሰላምታ ጋር

የኦሮሞ ቄሮ”